7. እግዚአብሔር ግን ሳሙኤልን፣ “መልኩን ወይም ቁመቱን አትይ፤ እኔ ንቄዋለሁና። እግዚአብሔር የሚያየው፣ ሰው እንደሚያየው አይደለም። ሰው የውጭውን ገጽታ ያያል፤ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል” አለው።
8. ከዚያም እሴይ አሚናዳብን ጠርቶ በሳሙኤል ፊት እንዲያልፍ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር ይህንንም አልመረጠውም” አለው።
9. እሴይም ሣማን አሳለፈ፤ ሳሙኤልም፣ “እርሱንም እግዚአብሔር አልመረጠውም” አለ።
10. እሴይም ሰባቱን ልጆቹን በሳሙኤል ፊት እንዲያልፉ አደረገ፤ ሳሙኤል ግን፣ “እግዚአብሔር እነዚህንም አልመረጣቸውም” አለው።
11. ቀጥሎም እሴይን፣ “ልጆችህ እነዚሁ ብቻ ናቸውን?” ሲል ጠየቀው።እሴይም፣ “የሁሉም ታናሽ ገና አልመጣም፤ ነገር ግን በጎች እየጠበቀ ነው” ብሎ መለሰ።ሳሙኤልም፣ “በል ልከህ አስመጣው፤ እስኪመጣ ድረስ አንቀመጥምና” አለው።
12. ስለዚህ ልኮ አስመጣው፤ እርሱም ደም ግባት ያለው፣ ዐይኑ የሚያምርና መልከ መልካም ነበረ። እግዚአብሔርም፣ “የመረጥሁት ይህ ነውና ተነሥተህ ቅባው” አለው።
13. ሳሙኤልም የዘይቱን ቀንድ ወስዶ በወንድሞቹ ፊት ቀባው። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር መንፈስ በዳዊት ላይ በኀይል መጣ፤ ሳሙኤልም ወደ አርማቴም ሄደ።
14. የእግዚአብሔር መንፈስ ከሳኦል ስለ ራቀ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ ያሠቃየው ነበር።
15. የሳኦል አገልጋዮችም እንዲህ አሉት፤ “እነሆ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የታዘዘ ክፉ መንፈስ እያሠቃየህ ነው።
16. እንግዲህ በገና መደርደር የሚችል ሰው እንዲፈልጉ፣ ጌታችን በፊቱ የሚቆሙትን አገልጋዮቹን ይዘዝ፤ ከዚያም ከእግዚአብሔር የታዘዘው ክፉ መንፈስ ባንተ ላይ በሚመጣ ጊዜ በገና ይደረድርልሃል፤ ደኅናም ትሆናለህ።”
17. ስለዚህ ሳኦል አገልጋዮቹን፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችል ሰው ፈልጋችሁ አምጡልኝ” አላቸው።
18. ከአገልጋዮቹም አንዱ፣ “መልካም አድርጎ በገና መደርደር የሚችለውን የቤተ ልሔሙን የእሴይን ልጅ አይቻለሁ፣ እርሱም ጀግናና ተዋጊ ነው፤ በአነጋገሩ አስተዋይና የደስ ደስ ያለው ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው” ብሎ መለሰ።
19. ከዚያም ሳኦል፣ “ከበጎች ጋር ያለውን ልጅህን ዳዊትን ላክልኝ” ሲል መልክተኞችን ወደ እሴይ ላከ።
20. እሴይም እንጀራና በወይን ጠጅ የተሞላ አቁማዳ በአህያ አስጭኖ፣ የፍየል ጠቦትም አስይዞ ልጁን ዳዊትን ወደ ሳኦል ላከው።
21. ዳዊት ወደ ሳኦል መጥቶ አገልግሎቱን ጀመረ፤ ሳኦልም እጅግ ወደደው፣ እርሱም የሳኦል ጋሻ ጃግሬ ሆነ።
22. ከዚያም ሳኦል፣ “ዳዊትን ወድጄዋለሁና ከእኔ ዘንድ ሆኖ እንዲያገለግለኝ ፍቀድልኝ” ብሎ ወደ እሴይ ላከ።
23. ክፉው መንፈስ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሳኦል ላይ በሚመጣበት ጊዜ፣ ዳዊት በገናውን ይዞ ይደረድር ነበር፤ ሳኦልም ይሻለው ነበር፤ ክፉውም መንፈስ ከእርሱ ይርቅ ነበር።