1. አንድ ቀን የሳኦል ልጅ ዮናታን ወጣት ጋሻ ጃግሬውን፣ “ና በሌላ በኩል ወዳለው የፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር እንሻገር” አለው። ይህን ግን ለአባቱ አልነገረውም ነበር።
2. ሳኦልም በጊብዓ ዳርቻ መጌዶን በተባለ ስፍራ ከአንድ የሮማን ዛፍ ሥር ሰፍሮ ነበር፤ ስድስት መቶ ያህል ሰዎችም አብረውት ነበሩ፤
3. ኤፉድ ይለብስ የነበረውም አኪያ በመካከላቸው ነበር። እርሱም በሴሎ የእግዚአብሔር ካህን የነበረው የዔሊ ልጅ፣ የፊንሐስ ልጅ የኢካቦድ ወንድም የአኪጦብ ልጅ ነበር። ዮናታን አለመኖሩን ግን ያወቀ ሰው አልነበረም።
4. ዮናታን ወደ ፍልስጥኤማውያን ጦር ሰፈር ለመሻገር በፈለገበት መተላለፊያ ግራና ቀኝ አንዱ ቦጼጽ ሌላው ሴኔ የተባሉ ሁለት ሾጣጣ ዐለቶች ነበሩ።
5. አንዱ ዐለት በስተ ሰሜን በኩል በማክማስ አንጻር፣ ሌላው ደግሞ በስተ ደቡብ በኩል በጊብዓ አንጻር ይገኝ ነበር።