13. ሳሙኤልም እንዲህ አለ፤ “የማይገባህን አደረግህ፤ አምላክህ እግዚአብሔር የሰጠህን ትእዛዝ አልጠበቅህም፤ ጠብቀኸው ቢሆን ኖሮ፣ መንግሥትህን በእስራኤል ላይ ለዘላለም ባጸናልህ ነበር፤
14. አሁን ግን መንግሥትህ አይጸናም፤ እነሆ፣ እግዚአብሔር እንደ ልቡ የሚሆንለትን ሰው አግኝቶአል፤ አንተ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመጠ በቅህም፣ እርሱን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መርጦታል።”
15. ከዚያ በኋላ ሳሙኤል ከጌልገላ ተነሥቶ በብንያም ግዛት ወዳለው ወደ ጊብዓ ወጣ። ሳኦልም አብረውት የነበሩትን ሰዎች ቈጠራቸው፤ ብዛታቸውም ስድስት መቶ ያህል ነበረ።
16. ፍልስጥኤማውያን በማክማስ ሰፍረው በነበረበት ጊዜ ሳኦል፣ ልጁ ዮናታንና አብረዋቸው የነበሩት ሰዎች በብንያም ግዛት በምትገኘው በጊብዓ ነበሩ።
17. በሦስት ምድብ የተከፈሉ ወራሪዎች ከፍልስጥኤማውያን ሰፈር ወጡ፤ አንዱ ምድብ በሦጋል ግዛት ወደሚገኘው ወደ ዖፍራ አቀና፤
18. ሌላው ወደ ቤትሖሮን፣ ሦስተኛው ደግሞ በምድረ በዳው ትይዩ ካለው ከስቦይም ሸለቆ ቍልቍል ወደሚያሳየው ድንበር ዞረ።
19. ፍልስጥኤማውያን፣ “ዕብራውያን ሰይፍ ወይም ጦር ለራሳቸው አይሥሩ” ብለው ስለ ነበር፣ በመላው የእስራኤል ምድር ብረት ቀጥቃጭ አልተገኘም።
20. ስለዚህ እስራኤላውያን ሁሉ፣ ማረሻቸውንና ዶማቸውን ለማሾል፣ ጠገራቸውንና ማጭዳቸውን ለማሳል ወደ ፍልስጥኤማውያን ይወርዱ ነበር።
21. ማረሻና ዶማ ለማሾል የሚከፈለው ዋጋ ሁለት ሦስተኛ ሰቅል ሲሆን፣ መንሽና ጠገራ እንዲሁም የበሬ መንጃ ለማሾል ደግሞ አንድ ሦስተኛ ሰቅል ነበር።
22. ስለዚህ ጦርነቱ በተደረገበት ዕለት ከሳኦልና ከልጁ ከዮናታን በስተቀር፣ አብረዋቸው ከነበሩት ወታደሮች መካከል ሰይፍ ወይም ጦር የያዘ አንድም ሰው አልነበረም።
23. በዚያ ጊዜ አንድ የፍልስጥኤማውያን ጭፍራ ወደ ማክማስ መተላለፊያ ወጥቶ ነበር።